ጌታችን በእውነት ተነስቷል

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከዘላለማዊ ሞት ለማዳን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ከሞተ በኋላ ከመስቀል አውርደው ማንም ሰው ባልተቀበረበት በአዲስ መቃብር የአርማቲያሱ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ገንዘው በክብር ቀብረውታል። በአይሁድ አሳሳቢነት ታላላቅ ድንጋይ በመቃብሩ ላይ ተገጥሟል። መቃብሩም በጠባቂዎች እንዲጠበቅ ተደርጎል።ማቴ 27፥59

ንጉሥ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር ይላል አሁን እነሳለሁ፣ መድኃኒት አደርጋለሁ፣ በእርሱም እገለጣለሁ››መዝ 11፥5 ያለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነስቷል። ማቴ 28፥1 በሌሊት ወደ መቃብሩ ገሥግሰው የሄዱት ሴቶች ይኽን ታላቅ የምስራች ለመስማትና ለማየት የታደሉ ሲሆን ለደቀ መዛሙርቱ የትንሣኤውን የምስራች አብሣሪ ለመሆንም በቅተዋል::

ደቀ መዛሙርቱ በሰሙት ነገር በጣም ተገርመዋል። ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሮጠው ወደ መቃበሩ ቢሄዱ እንደተባለውም መቃብሩን ባዶ ሆኖ አገኙት። ይህንን የምስራች ሰምተው በመገረም ከኢየሩሳሌም ተነስተው ቤታቸው ወዳለበት ወደ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩት ቀለዮጳና ሌላው ደቀ መዝሙር የተባለው ሉቃስ ስለሰሙት በመገረም በጌታ ላይ ስለተፈጸመው ግፍና የካሕናት አለቆች ስላደረሱበት መከራ እርስ በርሳቸው እየተነጋገሩ ይሄዱ ነበር። ምንም እንኳን ከልባቸው ሐዘን የተነሳ በፊታቸው ላይ ድካም ቢታይም በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስለደረሰው መከራ መነጋገር ግን አላቆሙም ነበርና ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንገድ ላይ ተገለጸላቸው። እነርሱ ግን ማንነቱን አላወቁም ነበረ።

ያዘኑትን የሚያጽናና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እነርሱ ቀርቦ ‹‹እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሯቸው እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው?›› ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱ ግን ‹‹አንተ ለኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህ? በእነዚህ ቀናት በዚህ የሆነውን አታውቅምን?›› ብለው በመገረም መልሰው ራሱን ጠየቁት። ጌታም ‹‹ይህ ምንድን ነው?›› አላቸው። በእግዚአብሔርና በሕዝብ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ስለነበረው መሢህ ካህናትና የካህናት አለቆች ለገዥዎች እንዴት አድርገው አሳልፈው እንደሰጡት መኳንንቶቻቸውም እንደሰቀሉት ይነግሩት ነበረ። እነርሱ ግን እስራኤልን ያድናል ብለው ተስፋ አድርገን ነበር በማለት ብርሃናቸው መጨለሙን ተስፋቸው መደብዘዙን የሚያሳይ አነጋገር ይናገሩ ነበር።

ይሁን እንጂ በጣም ያስገረማቸው በዛሬው ዕለት በሌሊት ወደ መቃብሩ ሄደው የነበሩ ሴቶች መቃብሩ ባዶ ሆኖ እንዳገኙትና ሕያው ነው የሚል የመላእክትን ድምጽ መስማታቸውንም እንደነገሯቸው ነገሩት። እርሱ ራሱ ስለ ተቀበለው መከራ ሕማምና ስቃይ በመስቀል ላይ መሰቀሉን የነገሩትን ካዳመጣቸው በኋላ በነቢያት ትንቢት የተነገረውን ባለማስተዋላቸው ገሰጻቸው። በእርሱ ላይ የተፈጸመው ህማም፣ መከራና ሞት፣ ኋላም ከሞት መነሳትና በክብር መገለጥ ሁሉ ቀድሞ የተነገረ መሆኑን ከሙሴ መጻሕፍትና ከነቢያት ትንቢት በዝርዝር ገልጦ ተርጉሞ አስረዳቸው።

ወደሚኖሩበት መንደር ሲቃረቡ ጊዚው መሽቶ ነበረና ወደ ሩቅ የሚሄድ መስሏቸው ወደ ቤታቸው እንዲገባ ለመኑት። ከእነርሱ ጋር ሊያድር ገባ። ማዕድም አቅርበው ባረኮ ቈርሶ በሰጣቸው ጊዜ ዓይናቸው ተከፈተ። ጌታ መሆኑንም አወቁት። እርሱ ግን ተሰወራቸው። የመጻሕፍትን ቃል ገልጦ ሲያብራራልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረን? ተባባሉ። እንደርም ሳይሉ በዚያችው ሰዓት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። የምሥራቹን ላልሰሙት ለማሰማት ደቀ መዛሙርቱም ተሰብስበው ወዳሉበት ገቡ ‹‹ጌታ በእውነት ተነስቷል ለስምኦንም ታይቷል›› እያሉ እየተነጋገሩ ሳለ አገኙዋቸው። እነርሱም በመንገድ የሆነውንና እንጀራ ቈርሶ በሰጣቸው ጊዜ እንደተገለጸላቸው ተረኩላቸው።

ከሁለቱ ደቀ መዛሙርት የምንማረው ብዙ ትምህርት አለ ክርስትና የሕይወት ጉዞ ለመልካም ነገር አለመዘግየትን በክርስትና የሕይወት ጉዞ መከራ መስቀሉን ማሰብን ቅዱስ ቃሉን በማስተዋል መስማትን ገንዘብ ማድረግን እንማራለን ሁለቱ ደቀ መዛሙርት በጉዞቸው ላይ ሳሉ የመዛልና የድካም መንፈስ ቢታይባቸውም አዳኝ መድኃኒት ስለሆነው ስለ ክርስቶስ ከመነጋገር ስለ እርሱ ከማሰብ የገታቸው ነገር አልነበረም። እኛም በዚህ ዓለም ስንኖር በሕይወታችን ልዩ ልዩ ውጣ ውረድ ቢያጋጥመንም በሕይወታችን ጉዞ ሁሉ ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል የተቀበለውን መከራ ልናስብ ልንዘክር ይገባል። በሁለቱን ደቀ መዛሙርት መካከል የተገኘ ጌታ በእኛም መሃል ይገኝ ዘንድ ሕይወታችንን ሁሉ ለእርሱ ልንሰጥ ይገባል። እርሱ ወደ እኛ ሕይወት እንዲገባ የልቦናችንን በር በንስሐ ቁልፍ ልንከፈተው ይገባል። ያን ጊዜ ብንደክምም የምሥራቹን ላልሰሙት ለማሰማት የበረታን እንሆናለን። ጌታም በእውነት ተነስቷል ብልን ያለጥርጥር እንመሰክራለን። ለዚህም ጸጋ የአምላካችን ያበቃን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን:: አሜን!

Donate