ሆሳእና በአርያም!

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከዘላለማዊ ሞት የማዳን ሥራ ለመፈጸም ጥቂት ቀናት ሲቀሩት በነቢያት የተነገረው ትንቢትና በብሉይ ኪዳን የነበረው ምሳሌ ይፈጸም ዘንድ በአህያይቱና በውርንጫው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱና ብዛት ያለው ሕዝብ ‹‹ሆሳዕና በአርያም›› እያሉ በመዘመር ሰማያዊ አዳኝ መሆኑን መስክረው ተቀብለውታል። ሆሳዕና ማለት አሁን አድን ማለት ነው፡፡

በነቢዩ በዘካርያስ 9፥9 የተነገረው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ‹‹በፊታችሁ ወዳለች መንደር ሂዱ በዚያም የታሰረች አህያ ውርንጫም ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ አላቸው›› ማቴ 21፥2። አህያዋ ከነውርንጫዋ ነጻነቷን ተገፋ የለመለመ ሣር እንዳትበላ፣ የጠራውን ውሃ እንዳትጠጣ፣ ታስራ እንደነበረ ሁሉ የሰው ልጅ ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን በሰይጣን አገዛዝ ሥር ወድቆ፣ ነጻነቱን አጥቶ፣ ጸጋው ተገፎ፣ ክብሩ ጐስቁሎ፣ በእግረ አጋንንት ይረገጥ ነበር።

ነቢዩ ቀደም ሲል ስለክርስቶስ ነጻ አውጭነት ‹‹ለታሰሩት መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን፣ እሰብክ ዘንድ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ ልኮኛል›› ኢሳ 61፥1 የሚለውን ቃል ለመፈጸም አዳምንና ልጆቹን ከኃጢአት እሥራት የሚፈቱበትና ወደ ቀደመ ክብራቸው የሚመለሱበት ጊዜ እንደደረሰ ለማስረዳት «ፈትታችሁ አምጡልኝ» አላቸው።

ይህም ‹‹…በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል። በምድር የምትፈቱት በሰማይ የተፈታ ይሆናል…›› ብሎ ሥልጣነ ክህነት የሰጣቸው ሐዋርያትና ከእነርሱም በኋላ የሚነሱ ካህናት ሰዎችን ከኃጢአት እሥራት እየፈቱ ነጻ እያወጡ ወደ እርሱ እንዲያቀርቡና ለእግዚአብሔር መንግስት የተገቡ እንዲሆኑ የተሰጠ ኃላፊነትን ያመላክታል፡፡

በዓለማችን ላይ ለክብር መግለጫ የተከበሩ ሰዎች የሚቀመጡባቸው የተለያዩ እንሰሳት ቢኖሩም በዚህ እለት ክርስቶስን የተቀመጠባት አህያ ነበረች። ለዚህም የተነገረ ትንቢት ነበረ። ትንቢቱ፦ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው። ትሁትም ሁኖ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱም ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል የሚለው ቃል ነው።

በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ነቢያት መጪው ዘመን የመቅሰፍት፣ የመዓት፣ የመከራ ዘመን መሆኑን ለመግለጥ ራቁታቸውን ሆነው በፈረስ ላይ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ሲታዩ የሰላም የደስታ የምህረትና የቸርነት ዘመን ሲመጣ ነጭ ልብስ ለብሰው በአህያ ላይ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው በአደባባይ ይታዩ ነበር።

ጌታችንም ሥርዐተ ነቢያትን በመጠበቅ ሕዝቡም በሚያውቀው ትውፊት በሰውና በአግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ በመስቀል የሚፈርስበት የእግዚአብሔር ምህረት ለሰው ልጅ ሊሰጥ የተቃረበበት ጊዜ መቃረቡን ለመግለጽ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቷል፡፡

ጌታችን በክብር ሆኖ ወደኢየሩሳሌም ሲገባ የፋሲካን በዓል ለማክበር ከየአገሩ የመጡ፣ ከሞተና ከተቀበረ በኋላ በአራተኛው ቀን ጌታችን ከሞት ያስነሳውን አልአዛርን ለማየት የተሰበሰው ብዛት ያለው ሕዝብ የዘንባባ ዝንጣፊና የለመለመ ቅጠል በመያዝ ልብሳቸውን በየመንገዱ በማንጠፍ ‹‹በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው፣ በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር›› እያሉ ሰማያዊ አዳኝ መሆኑን አውቀው በክብር ታላቅ በሆነ አቀባበል ተቀብለውታል።

ዘንባባ የሰላም፣ የደስታ፣ የድል አድራጊነት ምልክት ነው። አብርሃም ኮሎዶጎምርን ድል ባደረገ ጊዜ የዘንባባን ዝንጣፊ ይዞ እግዚአብሔርን አመስግኗል። ዮዲት ሆልኒፎሮስን ድል ባደረገች ጊዜ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዛ ድል አድራጊነቷን ገልጻለች። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን ዲያቢሎስን ድል የሚያደርግበት፣ የሰውን ልጅ ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ የሚያወጣበትና የሚያድንበት ጊዜው ተቃርቦ ነበርና ድል አድራጊነቱን ለመግለጽ ዘንባባ ይዘው ሆሳእና በአርያም እያሉ ተቀብለውታል።

ብዛት ያለው ህዝብ ከፊትና ከኋላ ሆኖ ህፃናት ሳይቀሩ ሆሳእና አያሉ ሲያመሰግኑ ያዩ ፈሪሳዊያን በቅንአት መንፈስ ተቃጠሉ። ለራሳቸው ክብር ሲጨነቁ የጌታ ክብር አልታይ አላቸው። ለራሳቸው ክብር፣ ዕውቀትና ዝና የሚጨነቁ ሰዎች የእግዚአብሔር ክብር አይታያቸውም። ስለዚህም እርሱን ለማመስገን አይችሉም። የእነርሱ አለማመስገን ብቻ ሳይሆን በሌሎች በመመስገኑ በቅንዓት መንፈስ ተቃጠሉ። የሚያመሰግኑትንም ለማስቆም ደቀ መዛሙርትህን ገስጻቸው አሉት።

ዛሬም በዘመናችን ፈሪሳዊ የሆነ ባሕሪይ ያላቸው ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የራሳቸውን ክብር የሚያስቀድሙ በአመጽና በሽንገላ የተሞሉ በግብር ፈሪሳዊ የሆኑ ሰዎችን ከቤተ መቅደስ ጀምሮ እስከ አወደ ምሕረቱ ማየት የተለመደ ነው። ምንም እንኳን ጸሐፍት ፈሪሳዊያንና መምህራን ሕጻናቱንን ደቀመዛሙርቱን እንዳያመሰገኑ ለማድረግ ቢፈልጉም ጌታ ግን እነርሱ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮሃሉ ብሎቸዋል።

በዚህ ዕለት የታሰረችውን አህያ ፈትታችሁ አምጡልኝ ብሎ እንድትፈታ እንዳደረጋት ሁሉ እኛም ከኃጢአት፣ ከበደል እሥራት ተፈተን ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። ሆሳእና በአርያም እያሉ ለጌታችን ክብር እንደሰጡት ሰዎች እኛም ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ለማክበርና ለማመስገን መሰለፍ አለብን።

‹‹እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ስሙንም ጥሩ በአሕዛብም መካከል ሥራውን አስታውቁ፣ ስሙ ከፍ ያለ እንደሆነ ተናገሩ። ታላቅ ስራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር ተቀኙ። ይኼንንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ›› ኢሳ 12፥4 ተብሏልና ስሙን አመስግነን ክብሩን ለመውረስ እንዲያበቃን የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን!

Donate