እነሆ ተወልዷል!

...

«ህፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፥ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል»ኢሳ 9፥6 የተባለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ሰማይና ምድር የማይችሉት አምላክ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነና በቤተልሔም ተወለደ። «የይሁዳ ምድር አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ ከይሁዳ ገዥዎች ከቶ አታንሽም ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና»ሚክ 5፥2 የሚል ትንቢት ተነግሮ ነበር። እነሆ ይህ ትንቢት እውን ሆነና የነገስታት ንጉሥ፥ የጌቶች ጌታ፥ የአማልክት ሁሉ አምላክ እንደ ቃል ኪዳኑ ተወለደ። ቅዱስ ኤፍሬም የነቢያት አገራቸው ቤተልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ ባንቺ ክርስቶስ ተወልዷልና ያለው ለዚህ ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ሲወለድ በቤተልሔም ዙርያ ብዙ ሰራዊተ መላእክት ከሰማይ ወርደዋል። ጨለማው በብርሃን ተሞልቷል። በዚያ ሌሊት መንጋዎቻቸውን ሲጠብቁ ለነበሩ እረኞች የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾ የምስራች ነግሯቸዋል።«እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል»ሉቃ 2፥11 በማለት የክርስቶስ ሰው መሆን ለሰው ልጆች ሁሉ ከሐዘን ወደ ደስታ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚወጡበት፤ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ የሚገኝበት መሆኑን ተናግሯል።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ይህን ድንቅ ምስጢር ቀደም ብሎ በራእይ ተመለከተ። ጌታ ኤፍራታ በተባለች በቤተልሔም ዱር እንደሚወለድ በመንፈስ ተረድቷልና «እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን»መዝ 131፥6 ሲል ተናገረ። እረኞቹ በቤተልሔም የጌታን መወለድ ከመልአኩ ሲሰሙ እንዋል እንደር ሳይሉ «እግዚአብሔር የገለጠልንን ይህን የሆነውን እንይ» ተባባሉ። ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙት» ሉቃ2፥16 ሰማይ ዙፋኑ ምድሩም የእግሩ መረገጫ የሆነ አምላክ በቤተልሔም ግርግም በከብቶች ዋሻ ውስጥ በጨርቅ ተጠቀለለ። ቅዱስ ያሬድ ይህን በተመለከተ «በግርግም ተኛ በጨርቅም ተጠቀለለ በድንግል ማሪያም ማኅፀን አደረ የዓለም መድኃኒት ጌታ ዛሬ ተወለደ.» ሲል ዘምሯል።

የምስራቅ ሰዎች የተባሉ ሰብአ ሰገልም የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው? ኮከቡን ከምሥራቅ ዓይተን ልንሰግድለት መጥተናል እያሉ በኮከብ ተመርተው ወደ ቤተልሔም መጥተዋል። ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስን ባገኙ ጊዜ በግንባራቸው ተደፍተው ሰግደውለታል። ሳጥናቸውን ከፍተው የነገሥታት ንጉሥ ነህ ሲሉ ወርቅ፣ እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት ለሆነው ክህነቱ ዕጣን፣ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዋናው ምክንያት መሪር ሞትን ሊቀበል ነውና ከርቤን ገብረውለታል። በዚህ የጌታ ልደት ላይ ሰራዊተ መላእክት ከሰማይ ወደምድር ወርደዋል። በአካባቢው ከሚኖሩ በሰው ዘንድ የሚናቁ እረኞች ይህን የምሥራች ለመስማትና ለማየት ተቀዳሚ ሆነዋል። የምሥራቅ ሰዎችም ጥበባቸው ከንቱ መሆኑን ተረድተው በጥበብ ሥራቸው ሳይመጻደቁ እውነተኛ የሆነውን ጥበብ በመፈለጋቸው የእግዚአብሔር ኃይሉና ጥበቡ የተባለውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አግኝተውታል። በዚህም የተዋረዱትን ሊያከብር የተናቁትን ከፍ ሊያደርግ ወደዚህ ዓለም እንደመጣ ታወቀ። በአንጻሩም አዋቂዎች ሆነው ሳሉ አለማወቃቸውን ለሚያውቁና እርሱን ለሚፈልጉ የሚገኝ አምላክ መሆኑንም አሳየ።

ትንቢተ ነቢያትን ከነትርጓሜው ጠንቅቀው የሚያውቁ መሲህ መቼና በየት እንደሚወለድ ሱባኤ የቆጠሩ ጸሐፍት ፈሪሳያውያን፣ መሲህ ሊወለድ ይህን ያህል ጊዜ ቀርቶታል እያሉ በሂሳብ ስሌትን በመጠቀም የሚዘረዝሩ ሊቃውንት፣ እለት እለት ከቤተ መቅደስ የማይለዩ ካሕናት በዚህ ዘመን ነበሩ። እነዚህ እዛው ኢየሩሳሌም ቁጭ ብለው ይህን ምስጢር ሊያዩ አልቻሉም። ይህን ድንቅ የሆነ አምላካዊ የማዳን ምስጢር ለማየት አልታደሉም። እነርሱ መድኃኒት የሆነው ክርስቶስን የጠበቁበት መንገድና እርሱ የመጣበት መንገድ የተለየ ሆነ። እነርሱ እንደ አንድ ነጻ አውጪ፥ ሰራዊት አሰልፎ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብሎ የሚመጣ አድርገውት ጠበቁት። እርሱ ግን ለጦርነት ሳይሆን ለፍቅር ሲል መጣ። ኢየሩሳሌምን ከሮማዊያን ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት የሚመጣ አድርገው ጠበቁት። እርሱ ግን አለሙን በሙሉ ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ ያወጣው ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣ። ቤተ መቅደሱ የሌቦች ዋሻ የወንበዴዎች መሸሻ ሆኖ ተገኝቷልና የአለምን ኃጢያት የሚያስተሰርይ የእግዚአብሔር በግ በቤተልሔም ዋሻ በከብቶች መኃል በበረት ተወለደ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ «የወለደችህ እናትህ እጅግ አስደናቂ ነች። ጌታ ወደእርሷ ገብቶ አገልጋይ ሆነ። መናገር የሚችል ሆኖ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ዝም አለ። የሁሉ እረኛ ሆኖ በእርሷ ውስጥ ገብቶ እንደ በግ ሆነ። እያለቀሰ ወጣ የእግዚአብሔር በግ የሰውን ልጆች ኃጢያት ለማስተስረይ በበጎች መሐል በበረት ተገኘ» ሲል በአድናቆት ገልጾታል።

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በሰው ልጅ ላይ የተፈረደውን ዘላለማዊ ሞት ታሪክ ብቻ እንዲሆን አድርጎታል። እርሱ ወደዚህ አለም የመጣው በዚህ ምድር ለመኖር አይደለም። የሰው ልጅ ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፉ የተነሳ ሞት ተፈርዶበት ነበረና ይህን ሞት የተፈረደበትን የሰውን ልጅ ከሞት ለማዳን መጣ። ቅዱስ ጎርጎርዮስ በደመናት መጋረጃ ተሰወረ፣ ከቅድስት ድንግል መድኅን ተወለደ፣ ጌታ ተገኘ እውነተኛ ፀሐየ ጽድቅ ወጣ እንዲል በጨለማ ላለነው ብርሃን ሆነን። ሕግ በመተላለፋችን በኃጢያት እርቀን ነበር። አሁን ግን በእርሱ ሰው መሆን ወደእራሱና ወደ አባቱ ቀረብን። «እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች»ኢሳ 7፥14 ተብሎ የተነገረው ትንቢት ሲፈጸም እንደስሙ ትርጓሜ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በተዋህዶ እንዳለ በልደቱ ታወቀ። አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ። «ቃል ሥጋ ሆነ፤ ጸጋና እውነትን ተሞልቶ በእኛ አደረ፤ ለአባቱ አንድ እንደሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን»ዮሐ 1፥14 የተባለውም ለዚህ ነው።

ይህን ድንቅ ምስጢር የተረዱ ቅዱሳን መላእክት ከሰዎች ጋር በኅብረት በመሆን ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ እያሉ ዘምረዋል። እኛም እግዚአብሔር ስላደረገልንና ሰለሚያደርግልን ሁሉ ነገር አመስግነን ክብሩን ለመውረስ እንዲያበቃን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤት በረከት አይለየን። አሜን!

Donate