ታማኝ አገልጋይ ማን ነው?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ሲያስተምር መንግስተ ሰማያት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለአንዱ አምስት፣ ለአንዱ ሁለት፣ ለአንዱ አንድ መክሊትን ሰጥቶ ወደ ሩቅ አገር የሄደን ባለጸጋ ሰውን ትመስላለች። ባለጸጋው መክሊቱን የሰጣቸው ለእያንዳንዳቸው እንደየአቅማቸው ነው። ሥራ እንዲሰሩበትና እንዲያተርፉበት ነው። መክሊቱንም ከሰጣቸው በኋላ ወደ እሩቅ አገር ሄደ። መክሊቱን የተቀበሉት ሰዎች በተሰጣቸው መክሊት መስራትና ማትረፍ ይጠበቅባቸው ነበር። መክሊቱ በኃላፊነት ሲሰጣቸው ተጠያቂነት ጭምር ነበረባቸው። ይህን የተረዱ አምስትና ሁለት መክሊት የተሰጣቸው ያቅማቸውን ያህል ሲንቀሳቀሱ አንድ መክሊት በአደራ የተቀበለው ግን ከጌታው የተቀበለውን መክሊት ቀበረ። ኃላፊነቱንና የተሰጠውን አደራ በሚገባ ለመወጣት ወጥቶ ወርዶ ከማትረፍ ይልቅ ስንፍናና አመጸኛነቱ እንዳይሰራ አድርጓታል። ማቴ 25፥ 15

የመክሊቱ ባለቤት ሰራተኞቹን ሊቆጣጠር ይመጣል

የገንዘቡ ባለቤት ከብዙ ጊዜ በኋላ ገንዘቡን ሊቆጣጠራቸው ወደ አገልጋዮቹ መጣ። ሲተሳሰባቸው ኃላፊነታቸውን በሚገባ የተወጡና ከተጣያቂነት ነጻ የወጡ አገልጋዮች ነበሩ። አምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ታማኝነቱን ጠብቆ በትህትና ወደ ጌታው ቀርቦ ጌታ ሆይ እነሆ አምስት መክሊት በአደራ ሰጥተህኝ ነበረ፣ እኔም ሌላ አምስት መክሊት አትርፌበታለሁ ብሎ አሥር መክሊት አስረከበ። ጌታውም «አንተ ታማኝና በጎ አገልጋይ በጥቂቱ አደራ ታምነሃልና በብዙ ክብር ላይ እሾምሃለው። ወደ ጌታህ ዘላለማዊ ደስታ ግባ» አለው። ባለ ሁለት መክሊት የተቀበለውም ሰው መክሊቱን ይዞ በታማኝነት ወደ ጌታው ቀረበ ጌታ ሆይ እነሆ ሁለት መክሊት በአደራ ሰጥተህኝ ነበረ በሁለቱ መክሊት ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት መክሊት አትርፌያለሁ አለው። ጌታም መልሶ «አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙም ላይ እሾምሃለው ወደ ጌታህም ዘለአለማዊ ደስታ ግባ» አለው። አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ አመጻኛ ነበር። ገንዘቡን ወደሰጠው ጌታ የቀረበው በትህትና ሳይሆን በትዕቢት ነበር። መክሊቱ ከመቅበር ይልቅ ቀድሞውንም አልቀበልም ቢል ይችል ነበር። ለሌላ አገልጋይ መክሊቱ ተሰጥቶ ትርፍ ባመጣ ነበረ። እርሱ ግን ጌታውን አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንክበት የምትሰበስብ ጨካኝ መሆንህን አወቅኩ ስለዚህ ፈራሁ የሰጠህኝን አደራ ወስጄ በመሬት ውስጥ ቀበርኩ አለ። በዚህን ጊዜ ጌታው ተቆጣ እንዲህም አለው አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ እኔ ካልዘራሁበት የማጭድ ካልበተንኩበት የምሰበስብ መሆኔን ማን ነገረህ? ይሄን ካወቅህ መክሊቱን ለምን ተቀበልክ? የማትነግድበትና ፍሬ የማታፈራበት ከሆነ መክሊቴን ለምን ተቀበልክ? ለሚሰሩና ለሚያተርፉ አገልጋዮች በሰጠሁት ነበር አለው። ጌታው አገልጋዮቹን ጠራቶ ይሄንን ሃኬተኛ ክፉ ባሪያ እጁንና እግሩን አስራችሁ ወደውጭ አውጥታችሁ ጣሉት ብሎ ፈረደበት።

ፍጹም ስጦታ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው

የመክሊቱ ባለቤት የተባለ እግዚአብሔር ነው። የእግዚአብሔር ያልሆነ በምድር ላይ አንዳች ነገር የለም። በባሕሪው ለጋሽና ቸር የሆነ አምላክ በመሆኑ ለሰው ልጆች ያልሰጠው ስጦታ የለም። ከሁሉ በላይ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን ልጁን ከሞት ያድነን ዘንድ የሰጠን ስጦታ ወደር የማይገኝለት ታላቅ ስጦታ ነው። በዚህ ስጦታው ምን ያህል እንደሚወደንና እንደሚያፈቅረን ያየንበት መስታወት ነው። «የእግዚአብሔር ስጦታ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት ነው» ሮሜ 6፥23። ይህን ታላቅ የሆነው የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ሥራውን ይሠሩ ዘንድ መክሊት ሆኖ የመሪነት፣ የአስተዳዳሪነት፣ የመጋቢነት፣ የጠባቂነት፣ ሥልጣንና ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር የተሰጣቸው ሰዎች አሉ። ይህም የአገልግሎት መክሊት ራስን ከማዳን ጀምሮ ሌሎችን ወደ ድኅነትና ወደዘላለማዊ መንገድ እንዲመጡ በጨለማ ላሉት ብርሃን ሆኖ መገኘት ይጠይቃል። መክሊቱም በሥርዓትና በአግባቡ የሚያዝ ንግዱም ስርዓታማ መሆን አለበት። 2ኛ ተሰ 3፥6-11

የሚሰጠንን መክሊት መልሰን ማስረከብ ዋጋ አለው

ቤተ ክርስቲያንን ያገለግሉ ዘንድ የኃላፊነት መክሊቱን ከተቀበሉት ከፓትርያርክ እስከ አፄ ኆኅት ካሉት ጀምሮ በአርባና በሰማንያ ቀን ልጅነትን እስከተቀበልነው ድረስ እግዚአብሔር እንደ አቅማችንና እንደጸጋችን የሰጠን ሥጦታ አለ። ሐይማኖታችን፣ ሥርዓታችን የተሰጡን መክሊቶች ናቸውና በሚገባ ልንይዝና ልንጠብቃቸው ይገባል። ጌታ ዕንቁዎቻችሁን በእርያ ፊት አታስቀምጡ ያለው ለዚህ ነው። ዕንቁ የሆነው መክሊት ሐይማኖታችንና ሥርዓታችን ነው «ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ» ተብሏል ራእ 3፥11። ሐይማኖታችንን ልንጠብቅ በሥርዓትም ልንጎዝ ያስፈልጋል። ቀኖናዊ የሆነውን አጥር የሚያፈርሱትን በመለየት መክሊት የሆነውን ጸጋችንን በሚገባ ልንይዝ ይገባል። መክሊቱን ወስዶ እንደቀበረው ሰው እኛም ጸጋ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንዳይሰራና ለሌሎች እንዳንተርፍ የሚያደርገንን ሥራ በንስሐ ሕይወት ራሳችንን ልንመረምር ይገባል። የተሰጠንን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት፣ አትራፊ ባለመክሊቶች ለመሆን፣ ከተጠያቂነት ለመዳን በመንፈሳዊ ሕይወታችን በመትጋት ፍሬ ሐይማኖት ማፍራት ይጠበቅብናል። ገላ 5፥22 እነርሱም ፍቅር፣ ሰላም በጎነት ናቸው።

የተሰጣቸው መክሊት ይብዛም ይነስም የማያተርፉበት ሁሉ ይጠየቃሉ። በጎቼን ጠብቅ ተብሎ ያልጠበቀ፣ ጠቦቶቼን አሰማራ ተብሎ ያላሰማራ፣ መክሊቱን ከቀበረው ሰው በላይ ይጠየቃል። ክርስቶስ ይህን የሥልጣነ ክህነት መክሊት ለሐዋርያው ሲሰጥ ትወደኛለህ? ብሎ ጠይቆ እንደሚወደው ካረጋገጠ በኋላ ነው። ከሹመት በፊት ፍቅር ካልቀደመ ሥልጣን ብቻውን ጨካኝ ያደርጋል፤ ምን አለብኝነትን ይፈጥራል። ባልተጠሩበትና ባልተሾሙበት ቦታ መገኝት ያመጣል። ሊያተርፋ ይቅርና የተሰጣቸውን መክሊት ለማስረከብ የማይችሉ፣ በጎቹ በተኩላ ሲበሉ፣ ለመታረድ ሲነዱ፣ ከአራጆቹ ጋር ሲደራደሩ የሚገኙ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ ተጠያቂነታቸውን የዘነጉ ቅጥረኞች የመክሊቱ ባለቤት ሲመጣ መልሳቸው ምን ይሆን? በጊዜያችን ባለመክሊቶች የተሰጣቸውን መክሊት እንኳን መልሰው ለማስረከብ የማይችሉ ሆነው እየታዩ ነው። እነዚህ አንድ መክሊት ተሰጥቶት ምድርን ቆፍሮ ቀብሮ ባለቤቱ ሲመጣ መልሶ ያስረከበውና ክፉ አገልጋይ ከተባለው ሰው ይልቅ የከፉ ናቸው።

ቀደምት አባቶቻችን የሕይወት መስዋዕትነት ሳይቀር ከፍለው የተሰጣቸውን መክሊት አትርፈው ታማኝነታቸውን ጠብቀው በመገኘታቸው መክሊታቸውን አትርፈዋል። ቅዱስ ጴጥሮስ ቀለሜንጦስን፣ ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቲዎስን አምሳያቸው ያደረጉት በሕይወታቸው ጭምር ምሳሌ ስለሆኗቸው ነው። እነዚህ አባቶች መክሊታቸውን አብዝተው በመገኘታቸው ለክብር በቅተዋል። እኛም የእነዚህን አባቶች አሰረ ፍኖታቸውን መከተል ይገባናል። «የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሮቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሏቸው» ዕብ 13፥7 ይላልና። የተሰጠንን የሐይማኖት መክሊት በሚገባ ይዘን ለሌሎችም ተርፈን ለመገኘት እንዲያበቃን የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን። አሜን!

Donate