ሰው የለኝም

ብዙውን ጊዜ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ተስፋ ሲቆርጡ ከሚያሰሙት ድምጽ ውስጥ አንዱ ሰው የለኝም እኔ እንደሆንኩ ብቸኛ ነኝ የሚለው ነው። ወገን ዘመድ ኃይል ገንዘብ የለኝም የሚሉ ቃላትን ሲያዘወትሩ ይደመጣሉ። እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ቃላት ዝም ብለው የሚመጡ ሳይሆን ሰዎች ታመው የሚድኑ፣ አጥተው የሚያገኙ፣ ተርበው የማይበሉ፣ ወድቀው የማይነሱ፣ ተሰብረው የማይጠገኑ፣ ታስረው የማይፈቱ ሲመስላቸው፣ እንዲሁም ተሰደው በባዕድ አገር ሲንከራተቱ፣ ኑሮ ሲከብዳቸውና መከራው አልገፋ ሲላቸው ሁሉ የማያልፍ መስሏቸው ብዙ ሰዎች ተስፋ በሚቆርጡበት ጊዜ የሚደመጡ ቃላት ናቸው። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ቀኑ ይጨልምባቸዋል። ወዳጆቻችን ናቸው ያሏቸው ሰዎች ሲርቋቸውና ሲረሷቸው የበለጠ ውስጣቸው ይጎዳል። የብቸኝነት ሰሜት ይጫጫናቸዋል። ባዶነት ይሰማቸዋል። ከሰው ተፈጥረው ሰው እንዳልሆኑ ሰው የለኝም እያሉ ኑሯቸውን በሃዘንና ሕይወታችውን በቀቢጸ ተስፋ መምራት ይጀምራሉ።

ብዙውን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእንደነዚህ አይነት ሕይወት ውስጥ ያሉ ሰዎችን እስካሉበት ድረስ እየሄደ አስተምሯል፣ አጽናንቷል፣ አረጋግቷል። ተስፋቸውንም ብሩኅ አድርጓል። የታመሙትን ፈውሷል። የሚያለቅሱ ሰዎችንም እንባ አብሷል። በዚህም ተስፋው ጨልሞ በሞትና በሕይወት መካከል እየኖረ አሁንስ ተስፋዬ ማነው? ላለ ለሰው ልጅ ተስፋው እርሱ መሆኑን አሳይቷል። በዚህ ምድር ሲመላለስ ካደረጋቸው ገቢረ ተአምራት ውስጥ አንዱ ለሰላሳ ስምንት ዓመት በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ ተስፋ ቆርጦ የነበረን ሰው ማዳኑ በወንጌል ተጽፎ ይገኛል። ዮሐ 5፥1 ሰው የለኝም የሚለውን ተስፋ የመቁረጥ ንግግር የተናገረው ይህ ሕመምተኛ ነው። ይህ ሰው ቤተ ሳይዳ /የምሕረት ቤት/ በምትባል የውሃ መጠመቂያ ሥፍራ ድኅነትን ፈልገው ከሚሰበሰቡ ሕሙማን መካከል አንዱ ሰው ነው። በዚህ ሥፍራ መልአኩ ውሃውን ባናወጠ ጊዜ ቀድሞ ወደ መጠመቂያው የገባ በሽተኛ ካለበት ደዌ ይፈወስ ነበር። ጉልበትና ወገን ያለው ውሃው ሲናወጥ ቀድሞ እየገባ እየዳነ ሄዷል። ይህ ሰው ግን «ውሀው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያው ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል» በማለት ከጉልበት ጉልበት፣ ከዘመድ ዘመድ፣ ከገንዘብ ገንዘብ የሌለው ብቸኛ መሆኑን እራሱ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ድኅነትን ለማግኘት ካለመሰልቸትና ካለመታከት በትእግስት ሆኖ ከቤተ ሳይዳ ሳይለይ የእግዚአብሔርን ምህረት በተስፋ ሲጠባበቅ የነበረ ሰው ነበር፡፡

ተስፋ ቆርጠው የሚገኙ፣ ለችግራቸው መፍትሄ ያጡ፣ በጉልበት መድከምና ጤና በማጣት ተስፋቸው የደበዘዘ፣ በግፍ አገዛዝ ውስጥ ያሉ፣ አይዞህ ባይ የሌላቸውና በልዩ ልዩ ችግር የሚሰቃዩ ሰዎች፣ በእምነት ወደ እግዚአብሔር ሊቀርቡ ይገባል። እርሱ ለሚታመኑበት አምባ፣ መጠጊያና ተስፋ ነው። መሸሸጊያና መሰወሪያ ነው። ቅዱስ ዳዊት «እግዚአብሔር አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ አምላኬና መሸሸጋዬ ነህ በእርሱም እታመናለሁ» መዝ 90፥2 ያለው ስለዚህ ነው። ይህን ሰው በችግሩና በሕመሙ ሰዓት የሚራዳው የሚያጽናና የሚያበረታታ ሰው ባይኖረውም ጌታችን ወደዚህ ህመምተኛ መጥቶ ልትድን ትወዳለህ? ብሎ የጠየቀው ለብዙ ዘመናት በደዌ ተይዞ እንደተኛ ያውቅ ስለነበር ነው። ከእርሱ ዘንድ የተሰወረ ነገር ምንም አይኖርም። የሚሰማንን የሕመም ስሜት፣ በሕይወታችን የሚገጥመንን ውጣ ውረድ፣ ችግራችንንና ስቃያችንን ሁሉ ያውቀዋል። በእርሱ ዘንድ የእያንዳንዳችን ሕይወት የተገለጠ ነው። አስታዋሽ የለኝም ብለን እንማርር ይሆናል እርሱ ግን መቸም መች አይረሳንም። አልለቅህም ከቶ አልተውህም ያለው ስለዚህ ነው። ዕብ 13፥5

ስለዚህም በእርሱ ብቻ እንታመን። በዘመድ አዝማድ በሥልጣንና በሃብት በውበት መመካት ዋጋ የለውም።የእግዚአብሔር ቃል «...ራስ ሁሉ ለሕመም ልብ ሁሉ ለድካም ሆኗል። ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም ቊስልና እበጥ የሚመግልም ነው...» ኢሳ 1፥6 እንዲል ያልታመመ የሰው ክፍል የለም። ከእረኛው እስከ መንጋው፣ ከአለቃው እስከ ጭፍራው፣ ከመሪው እሰከ ተመሪው፣ ከሊህቅ እስከ ደቂቅ ያለው ሁሉ ታሟል። በመሆኑም ፈውስ ያስፈልገዋል። «በሽታውን የደበቀ መድኃኒት የለውም» እንዲሉ አለም በሙሉ በኃጢያት ደዌ ውስጥ ወድቆ ይገኛል። የሚፈውስና የሚያድን ሰው የለም። የሥልጣን ጥማት፣ ጭካኔ፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት፣ ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ ዘማዊነትና ስግብግብነት በምንኖርበት አለም ከመጠን በላይ ተንሰራፍተው የሚገኙ ደዌያት ናቸው።

ህመምተኛውን ሰው ልትድን ትወዳለህ? ሲለው «መዳንስ እወዳለሁ ግን ሰው የለኝም» በማለት ለመዳን ያለውን ፍላጐት በማሳየቱ በተዋህዶ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ተነስ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» ሲለው ሰላሳ ስምንት አመት የተሸከመችውን አልጋ ተሸክሞ ሄዷል። ሕይወታችን በአደጋ ውስጥ ሲገባ ዙሪያችን ሁሉ በፍርሃት ሲታጠር እግዚአብሔርን ብቻ ተስፋ እናድርግ። ያን ጊዜ እርሱ ከእኛ ጋር ይሆናል። እራሱ «እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህም» ዘፍ 28፥15 ይላል። እግዚአብሔር ሁል ጊዜም እንዳይተወን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን አሜን!

Donate