ሰላም ለእናንተ ይሁን

‹‹የሰላም አለቃ››ኢሳ 9፡6 ተብሎ የተነገረለት መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያሰማው የሰላም መልእክት ነው። ሰላም በዕለተ ዓርብ በመስቀሉ ላይ ተሰብኳል። በሲዖል ለነበሩት ነፍሳት የሰላም ነፃነት ታውጇል። ደቀ መዛሙርቱ ግን ጌታ በአይሁድ እጅ ተላልፎ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ የሚያዩትና የሚሰሙት ሰላም አሳጥቶ አስጨንቋቸዋል። የአይሁድ ማስፈራራት እያየለ መጥቶ ስለነበር ተበታትነው የነበሩ ተሰባስበዋል። ተስፋ ቆርጠው በራቸውን ዘግተው ተቀምጠዋል። በአይሁድ ዘንድ ግን በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለመጀመርያ ጊዜ ሞቶ የተቀበረው የክርስቶስ ጉዳይ አስፈርቷቸዋል። በመቃብሩ ላይ ታላላቅ ድንጋይ እንዲገጠም አስደርገዋል። መቃብሩ በማኅተም ታትሟል። መቃብሩ በጠባቂዎች እንዲጠበቅ ተደርጓል።

በተከታዮቹ ዘንድ ግን ‹‹ይነሣል›› የሚል እምነት አልነበረም። እነ ማርያም መግደላዊት ሽቱ ቀምመው ያዘጋጁት በሦስተኛው ቀን በመቃብሩ ላይ ሽቱ ለማርከፍከፍ ነበር። በሌሊት ገስግሰው ሲሄዱ ያስጨንቃቸው የነበረው ድንጋዩን ማን ያነሳልናል የሚል ነበር። ከመቃብሩ ሲደርሱ ያዩት ግን ድንጋይ ተንከባሎ ሁለት መላእክት ነጫጭ ለብሰው በመቃብሩ አንዱ በራስጌ ሌላውም በግርጌ ሆነው ተገለጹላቸው። ሞቱ በጣም ያስደነቃቸው ቅዱሳን መላእክት ‹‹ሕያውን ከሙታን ጋር ለምን ትሹታላችሁ በዚህ የለም ተነሥቷል›› ሉቃ 24፥6 ብለዋቸዋል። ማርያም መግደላዊት ከመቃብሩ አጠገብ ቆማ ስታለቅስ እራሱ ጌታ ተገልጾላት አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? ብሏታል። በስሟም ‹‹ማርያም›› ብሎ ሲጠራት በድምጹ አውቃ ‹‹ረቡኒ›› ብላዋለች። ትንሣኤውን እንድትናገር በታዘዘችው መሠረት ብትመሠክርም በሐዋርያት ዘንድ ለጊዜው ተቀባይነትን አላገኘችም ነበር። ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቃብሩ ሲሄዱ በአንዳንዶቹ ግን እንደ ቅዠትና የሃሰት ወሬ ተደርጎ ተቆጥሮ ነበር።

እምነት በሌለበት ቦታ ሁሉ ፍርሃት አለ። በፍርሃትና በጭንቅ ውስጥ ደግሞ ሰላም አትገኝም። ሰላም ከመንፈስ ፍሬ ውስጥ ተቀዳሚ ቦታ የሚሰጣት የእግዚአብሔር ጸጋ ናት። ገላ 5፥22 ቀደም ሲል በመካከላቸው ሳለ ለደቀ መዘሙርቱ ‹‹ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ››ዮሐ 1፥27 የሚል አምላካዊ ቃል ኪዳን ገብቶላቸው ነበር። የትንሣኤውን የምሥራች ካለማመናቸው የተነሣ በጥርጥር ውስጥ ተዘፍቀው በአይሁድ ዛቻ ደንግጠው የሚኖሩበትን ቤት ዘግተው ሳለ ለሁለተኛ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጾላቸው ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› አላቸው። በዚህ ወቅት ይኽ የቃል ኪዳን ተስፋ ተፈጽሟል።

‹‹ለክፉዎች ሰላም የላቸውም››ኢሳ 48,,22 እንዲል አይሁድ በክፋታቸው እራሳቸው ሰላም አጥተው የሰላም አለቃ የሆነውን ጌታ በመስቀል ላይ ሰቀሉት። ደቀ መዛሙርቱንም ማሳደድና ማስፈራራት ሥራቸው አደረጉት። ዛሬም በዓለማችን ላይ ለራሳቸው ሰላም አጥተው የሰውን ሰላም የሚያውኩ ብዙ ይገኛሉ። ብዛት ያላቸው ንጹሐን ሰዎች አረጋዊያንና ሕጻናት ሳይቀሩ ለእንግልት ሲዳረጉ ማየት የዚህ ዓለም አንዱ አሳዛኝ ገጽታ ነው። እንዲሁም ከፍርሃት፤ከጭንቅና ከመከራ የተነሳ በራቸውን ዘግተው በሚኖሩ ሰዎች ዓለማችን ተሞልታ ትገኛለች። እግዚአብሔር ለእነዚህ ሁሉ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ ይላል። ሰላሙን ለመቀበል የሰው ልጅ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል።

በመጀመሪያ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ በዝግ ቤት ሲገለጥ አብሯቸው ያልነበረው ቶማስ ስለጌታ ትንሣኤ ሲነግሩት አላመነም። ‹‹የችንካሩን ምልክት በአይኔ ካላየሁ፤ ጣቴንም ወደ ተቸነከረበት ካልጨመርኩ እጄንም ወደ ጎኑ ካላገባሁ አላምንም›› እስከማለት ደርሷል። ቶማስ እስከሞት ድረስ ለጌታችን የታመነ መሆኑን ተናግሮ ነበር። ዮሐ 11፥16 ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ይልቅ ያልተረዳውን ለመጠየቅ ወደ ኋላ የማይል ሐዋርያ ነበር። ዮሐ 14፣5 ቶማስ የጌታን ትንሳኤ በደቀ መዛሙርቱ ሲነገረው የተጠራጠረውን ለማመንና ለመቀበል ከብዶታል። በጦር የተወጋ ጎኑን የተቸነከረሩ እጆቹን ካላየሁ አላምንም ስላለ ጌታችን መደኃኒታችን ኢየሱስ ቀድሞ እንደተገለጸው በመካከላቸው ተገኝቶ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› አላቸው። ቶማስንም ተጠራጣሪ አትሁን ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን ንካ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ›› ባለው መሰረት የተቸነከሩ እጆቹን የተወጋ ጎኑን በመንካት ትንሳኤውን አምኖ ተቀብሎል። ‹‹ጌታዬ አምላኬም›› በማለት የክርስቶስን አምላክነትና ጌትነት መስክሯል። ያመነው አይቶና ዳስሶ ስለነበር ‹‹ብፁዓንስ ሳያዩ የሚያምኑ ናቸው›› ብሎታል። በዘመናችን እንደ ቶማስ ለማመን ሳይሆን ለመካድ የሚጠራጠሩ አሉ። እነዚህ ጌታን የሰቀሉትን አይሁድን ይመስላሉ። ብዙ ገቢረ ተአምራቱን ቢያዩም አላመኑበትም። በመስቀል ላይ እንደወንጀለኛ ሰቀሉት እንጂ።

ጌታችን በቤተልሔም ሲወለድ ሰላም በምድር ላይ መስፈኑ በመላእክት ተዘምሮ ነበር። አሁን በበለጠ በትንሣኤው እየተደጋገመ በጌታ ዘንድ ‹‹ሰላም ለሁላችሁ ይሁን›› የሚለው ምስራች ተሰበከ። የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ይህንን ሰላም ለሰው ልጅ ሁሉ የማዳረስ ሃላፊነት ተቀብላለችና በሁሉም መንፈሳዊ አገልግሎቷ ውስጥ ‹‹ሰላም ለሁላችሁ ይሁን›› የሚለውን የክርስቶስን መልእክት ታስተጋባለች። በትንሣኤው ውስጥ የተሰበከውን ሰላም በአገልግሎቷ ውስጥ ለልጆችዋ ‹‹እምይእዜሰ ኮነ ሰላም…. ከእንግዲህ ወዲህ ሰላም ሆነ›› እያለች ታበስራለች።

እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን ለልጆቹ የሰላም ድምጹን ያሰማል። አመጽ በሞላበት በዚህ ዓለም ውስጥ የሰው ዘር ከምን ጊዜውም በላይ በፍርሃት በጭንቅና በጥርጥር ውስጥ ይገኛል። ሰላማቸውን አጥተው በጭንቅ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ሰላምን ሊሰጣቸው ይፈልጋል። ሰላምን ለሚሻት እግዚአብሔር ፍጹም የሆነውንና እውነተኛውን ሰላም ለመስጠት ምንም አያግደውም። በጦር መሳርያ ብዛት በአመጽና በጥላቻ ሰላም አትገኝም። ስለ ሰላም ስለተወራ ሰላም አይመጣም። እውነተኛ ሰላም የሚገኘው ከእግዚአብሔር ብቻ ነውና ወደ እግዚአብሔር በእምነት መቅረብ ያስፈልጋል እርሱ ሰላማችን ነውና። ‹‹ኑ ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል …ሠይፋቸውን ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሳም ››ኢሳ 2፥5 ይላልና በሰላም ለመኖር የሰላም አምላክ የሆነውን እግዚአብሔርን መሻትና ያስፈልጋል።

ሰላም በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ እንድትገኝ ሕይወታችን ለእግዚአብሔር ማደሪያነት የተመቸ መሆን አለበት። ያን ጊዜ ሰላምን እያንዳንዳችን እናገኛለን። በፍጹም ልባችን ወደእርሱ እንቅረብ። ዛሬም ሰላም ለሁላችሁ ይሁን ሊለን አምላካችን በመካከላችን ይገኛል። የሰላምና የፍቅር አምላክ የሆነ አምላካችን ለሁላችንም ሰላምን ያድለን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። አሜን!

Donate