መስቀል ኃይላችን ነው

ከመስከረም 16 ቀን እስከ 25 ድረስ ያሉት ቀናት መስቀል የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው ለእኛ ለምናምን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው»1ኛ ቆሮ 1፥18 ብሏል። ይህ መልእክት በተላለፈበት ዘመን ይኖሩ የነበሩት የአብርሃም ዘሮች ነን የሚሉ አይሁድና ለሥጋዊ ጥበብ ከፍተኛ ቦታ ይሰጡ የነበሩ ግሪኮች የክርስትናን እምነት በራሳቸው አመለካከት ለመረዳት የሚሹ ነበሩ። የክርስቶስን የማዳን ጥበብ ለመረዳት አይሁድ በአይናቸው ተአምራትን ለማየት ሲሹ የጥበብ ሰዎች ነን የሚሉት በሥጋዊ ጥበብ የመስቀሉን ቃል ሊመራመሩ ፈልገዋል። ይህ ምስጢር ግን የሚገለጠው በእምነት ለሚፈልጉት ስለሆነ የመስቀሉ የማዳን ሥራ ከእነርሱ ሊሰወር ችሏል።

መስቀል በዘመነ ብሉይ በተለያዩ አገራት የወንጀለኛ መቅጫ ስለነበር እንደመርገም ምልክት ተደርጐ ይታይ ነበር። የፋርስ ሰዎች አርሙዝድ ብለው የሚጠሩት የመሬት አምላክ ሰዎች ሲያጠፉ በምድር ላይ የሚቀጡ ከሆነ ይህ አምላክ መቅሰፍት ያመጣል ብለው ስለሚያምኑ ወንጀለኛን ሰው በመስቀል ላይ መስቀል የተለመደ ነበር። ኋላ ላይ ይህ ቅጣት ወደ ግብፅ፣ አሶር፣ ግሪክና ሌሎችም አገሮች ተዛምቷል። በመስቀል ላይ የሚሰቅሉትን ሁሉ እንደ ርኩስ ይቆጥሩታል። ሮማውያን ሮማዊ የሆነ ዜግነት ያለውን ሰው ጥፋተኛ ነው ብለው የሞት ቅጣት ቢወስኑበትም ለዜግነቱ ክብር ሲሉ በመስቀል ላይ አይሰቅሉትም ነበር። ቅዱስ ጴጥሮስ በመስቀል ላይ ቁልቁል ሲሰቀል ቅዱስ ጳውሎስ አንገቱን በሰይፍ የተቀላው ሮማዊ ስለሆነ ነው።የኦሪቱም ሕግ በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነው ስለሚል መስቀል በአይሁድም ዘንድ የርግማን ምልክት ተደርጐ ይቆጠር ነበር። በኃጢአት የወደቀውንና በመርገም ሕይወት ውስጥ የነበረውን የሰውን ልጅ ከውደቀቱ አንስቶ ወደሰማያዊ አባቱ ሊያቀርበው የወደደ መድኃኔ ዓለም በዚህ የርግማን ምልክት በሆነው መስቀል ላይ ደሙን አፍሰሶ በመርገም ውስጥ የነበረውን ዓለም ከኃጢአት ነጻ አድርጎታል።

ምንም እንኳን አይሁድ በምቀኝነት ተነስተው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ላይ ቢሰቅሉትም፤ ሞትን ድል አድርጐ ተነስቶ ወደሰማይ ቢያርግም፤ የተሰቀለበት መስቀል ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራት ያደርግ ነበር። በዚህም አይሁድ በጣም ስለቀኑ መስቀሉን ከከተማ ውጭ በማውጣት ጉድጓድ ቆፍረው ቀብረውታል። በቦታው ላይም ቆሻሻ እንዲጣል በማስደረጋቸው ለሶስት መቶ አመታት ያህል የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ቆይቷል። የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግስት እሌኒ የጌታ መስቀል በኢየሩሳሌም ተቀብሮ ለብዙ ዘመናት መኖሩን ትሰማ ነበረና ልጄ ክርሰቲያን ቢሆን ከቁስጥንጥንያ ሄጄ ከተቀበረበት አስቆፍሬ አወጣዋለሁ ብላ ስእለት ተስላ ነበር። ልጅዋ ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ሲሆን ኢየሩሳሌም ሄዳ መስቀሉ ያለበትን ቦታ ፈልጋ ደመራ አስደምራ በማቀጣጠል ዕጣን ብታስደርግ መስቀሉ ያለበትን ቦታ የእጣኑ ጢስ በቀስት አምሳያ ተመልሶ ቦታውን ስላመላከታት መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት 10 ቀን መስቀሉን ልታገኝ ችላለች።

ቅዱስ ጳውሎስ እኛስ የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስ እንሰብካለን እንዲል በመሰቀሉ ላይ የተፈጸመውን ድኅነት ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ትገልጣለች። በዘመናት ሁሉ ውስጥ በማያቋርጠው የድኅነት ስብከቷ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሰለ ሰው ልጅ መከራ የተቀበለውን አምላክ ለዓለም ትሰብካለች። በባርነት ቀንበር ውስጥ ለነበሩ ነጻነት የታወጀበት፣ ሰይጣን የተሸነፈበትና ድል የተደረገበት፣ የፍቅር ማህተም የሆነው ደመ ማህተሙ የታተመበት፣ በሰውና በእግዚአብሄር መካከል የነበረው የጸብ ግድግዳ የፈረሰበት፣ የሰላምና የፍቅር ማሳይ መስታወት ነው። ስለዚህም ቤተክርስቲያን ለቅዱስ መስቀል ከፍተኛ ክብር ትሰጣለች። ከእግዚአብሔር ርቀው የነበሩ የቀረቡበት፣ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ያፈረበት እና የነቢያት ትንቢት ሁሉ ፍጻሜ ያገኘው በቅዱስ መስቀል ነው። በመሆኑም ምእመናን ይህንን ታላቅ በዓል በምናከብርበት ጊዜ ስለእኛ ሲል መድኃኔዓለም ክርስቶስ የከፈለልንን ታላቅ መስዋእትነት ከምንም በላይ ሁል ጊዜ ልናስበው ይገባል እርሱ ለእኛ ሲል ደሙን ካፈሰሰ እኛ ደግሞ በፍቅሩ ልንኖር ይገባናል።

እግዚአብሔር አምላካችን ከብርሃነ መስቀሉ ረድኤት በረከት ያካፍለን። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን። አሜን!

Donate